የናፍቆት ሰማዕት

by ሀይማኖት መስፍን

ETB 350.00

Condition: Like new
Category: Fiction
Language: Amharic
Edition: 1st Edition
Publication Year: 2018
Location: Addis Ababa (Bole)
Description

ምዕራፍ አንድ

የጎጃም ጽልመት

የጎጃም ምድር በዚያን ዘመን ገና የዘመናዊነት ድምጽ ሳይበሰርባት በተፈጥሮ ድንግል ውበት የደመቀች ነበረች። በተለይበሻሻት መንደር አፈሩ እንደ ደም የቀላ አየሩ ወዲህ እና ወዲያ እያወዛወዘ የካህናት ወረብ የሚወርቡ በሚመስሉ በባሕርዛፍ ዛፎች እና በብሳና ዛፎች ያሸበረቀች ውብ መንደር ናት። ክረምቱ ሲወጣ የሚታየው የአደይ አበባ ምንጣፍ ምድሪቱ የወርቅ ካባ የለበሰች ያስመስላታል።በዚህች ገነት በምትመስል ግን ደግሞ የኑሮ ቀንበር በከበዳት መንደር ዳርቻ ከአውራ ጎዳናው ወረድ ብሎ በትላልቅ ግራር እና ዋንዛ ዛፎች ተከበበች አንዲት ጎጆ ትገኛለች። የጎጆዋ አጥር በቁልቋል የተከበበ ሲሆን የሳር ክዳኗ በዘመን ብዛት ጠቆር ቢልም ከውስጥ የሚወጣው የፍቅር ሙቀት ግን ከቤተመንግስት ይልቅ ያስቀና ነበር

የቤቱ አባወራ አቶ አዳሙ፣ ቁመታቸው ዘለግ፣ ትከሻቸው ሰፋ ያለ፣ ፊታቸው በፀሐይ የጠቆረ ግን ደግሞ ቅንነት የሚነበብባቸው ታታሪ ገበሬ ናቸው፡፡ እጆቻቸው ከምድር ጋር በመታገል የሻከሩ ቢሆኑም፣ ልጆቻቸውን ሲያቅፉ ግን እንደ ሐር ይለሰልሳሉ። ባለቤታቸው ወይዘሮ አታለል፣ ስማቸው "አታለል" ይባል እንጂ ተንኮል የማያውቁ፣ የዋህ እና ታታሪ እናት ናቸው። ቀሚሳቸውን አገለድመው፣ በባዶ እግራቸው ወዲያ ወዲህ ሲሉ፣ የቤቱ ምሰሶ እርሳቸው እንደሆኑ ያስታውቃል። ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ነበር። ጠዋት ወጥቶ ማታ መግባት፣ ከአፈር ጋር መታገል፣ ዝናብ መጠበቅ። ነገር ግን፣ ሀብታቸው በጎተራ ሳይሆን በልባቸው ነበር። እግዚአብሔር የሰጣቸው ሦስት ፍሬዎች የኔወርቅ፣ መኳንንት እና ይበልጣል የድህነታቸው ማካካሻ ነበሩ።

የበኩር ልጃቸው የኔወርቅ፣ የአሥር ዓመት ልጅ ብትሆንም የአእምሮዋ ብስለት ከእድሜዋ ይልቅ ነበር። ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነቃ፣ መጀመሪያ የምታደርገው የእናቷን ሸክላ ማጠብ ነው። ገና ዶሮ ሳይጮህ ተነስታ፣ ቀዝቃዛውን ንፋስ እየቀዘፈች ከወንዝ ውሃ ትቀዳለች። ውበቷ እንደ ስሟ ወርቅ ነበር፤ ዓይኖቿ ትላልቅ፣ ጥርሶቿ እንደ ወተት የነጡ። አዳሙ "የእኔ እናት" እያለ ሲጠራት፣ የኔወርቅ ፊቷ በፈገግታ ይሞላል። መኳንንት እና ይበልጣል ደግሞ የሰባት እና የአምስት ዓመት ልጆች ናቸው። መኳንንት፣ አባቱን ለመምሰል የሚጥር፣ ገና በጠዋቱ "በሬ ልጥመድ" ብሎ የሚያስቸግር ጠንካራ ልጅ ነው። ይበልጣል ደግሞ የቤቱ የመጨረሻ (የዚያን ጊዜ)፣ ተጫዋች፣ የእናቱ ቀሚስ ስር የማይጠፋ ምርጥ ልጅ ነበር። ምሽት ሲሆን፣ ፀሐይዋ ወደ ማደሪያዋ ስትጠልቅ፣ አዳሙ ከእርሻ፣ ልጆቹ ከጨዋታ፣ አታለል ከጓሮ ስራ ተሰባስበው እሳት ዳርይቀመጣሉ። የኩበት ጭስ ይጨሳል። አታለል የቆላችው ገብስ ወይም የቆላችውን የቦቆሎ አሻሮ ቆሎ ይቀርባል።

"አባዬ ዛሬ እኮ ጥንቸል አየሁ!" ይላል መኳንንት በጋለ ስሜት።
"እኔ ደግሞ ለቀበሮዋ ዘፈንኩላት" ይላል ይበልጣል እየተንተባተበ።

ቤቱ በሳቅ ይሞላል። ላምባው አልቆ መብራቱ ብልጭ ድርግም እያለ የቤቱን ጨለማ ሲገፈው፣ የእነ አዳሙ ሳቅ ደግሞ የኑሮን ጨለማ ይገፈው ነበር። ያቺ ጎጆ፣ በጎጃም ምድር ላይ ያለች ትንሽ ገነት ነበረች። ነገ ምን እንደሚመጣ፣ እጣ ፈንታ ምን እንደቋጠረችባቸው የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ጥቅምት ወር ገባ ። አዝመራው አሽቶ፣ ነፋሱ ተለውጦ፣ ምድሩ የመኸር ሽታ ማምጣት ጀመረ። ነገር ግን በዚያች አመት፣ ነፋሱ ያዘለው የምስራች ሳይሆን የመርዶ ዜማ ነበር። አየሩ ከበደ። ሰማዩ የቀድሞ ጥራቱን አጣ።ወሬው እንደ እሳት ተዛመተ። "በታችኛው አጢማር በሚባለው ቀበሌ በሽታ ገባ" ተባለ።

"ወባ ነው" አሉ። ይላሉ አንዳንዶቹ

''አይደለም፣ የአምላክ ቁጣ ነው'' ይላሉ ደግሞ ሌሎቹ።

አዳሙ ይህንን ሲሰማ፣ ማታ በሩን ሲዘጋ ጠንከር አድርጎ የሚዘጋው፣ ያንን ክፉ መንፈስ ከደጃፉ የሚያስቀረው እየመሰለው ነበር። አንድ ማክሰኞ ምሽት። የኔወርቅ እንደተለመደው በትንሿ ማድጋ(እንስራ) ለማታ የሚሆን ውሃ ከሻሻት ወንዝ ቀድታ መጣች። ማድጋውን አውርዳ ስታስቀምጥ ግን እጆቿ ይንቀጠቀጡ ነበር።

"እማዬ...'' አለች ድምፅዋ እየላላ።

"አመመኝ።"

አታለል ከምድጃው ተነስታ የልጅቷን ግንባር ዳሰሰቻት።

እሳት! የሚለበልብ እሳት።

"ምነው የኔ ልጅ? ምንሽን ነው?'' አለች አታለል ደንግጣ።

"ብርድ ብርድ አለኝ... እግሮቼን ቆረጠኝ" አለች የኔወርቅ። ጥርሶቿም ይንቀጫቀጩ ነበር።

ያ ምሽት የቤተሰቡ የደስታ ፀሐይ የጠለቀችበት የመጨረሻ ምሽት ሆነ። አዳሙ ካባውን አውልቆ ደረበላት። አታለል እሳቱን አቀጣጠለች። የልጅቷ ሰውነት ግን እየባሰበት ሄደ። ትኩሳቱ ሲጨምር፣ የኔወርቅ በቃላት የማይገለጽ ቅዠት ውስጥ ገባች።

"አባዬ አትሂድ... ጅቡ መጣ...'' እያለች ትጮሃለች።
በማግስቱ፣ ውቢቷ የኔወርቅ መልክ ተቀየረ። ዓይኖቿ ወደ ውስጥ ገቡ። ከንፈሮቿ ደረቁ። አዳሙ ወደ መንደሩ ጤና ጣቢያ ለመውሰድ ፈለገ፣ ግን ጤና ጣቢያው ሩቅ፣ መንገዱ አስቸጋሪ፣ ህክምናውም ውድ ነበር። ባህላዊ መድኃኒቶችን ሞከሩ። ፌጦ ተወቀጠ፣ ነጭ ሽንኩርት ተጨቅጭቆ ተሰጣት ፣ ጸበል ተረጨ። በሽታው ግን "እምቢ” አለ።

በሦስተኛው ቀን አመሻሽ ላይ፣ የኔወርቅ አቅሟ ተሟጠጠ። አልጋው ራስጌ ተቀምጣ ታለቅስ የነበረችው አታለል፣ የልጅቷ ትንፋሽ ሲቀየር አየች።

"የኔወርቅ... የኔወርቅ..." አለች አታለል በሹክሹክታ።

የኔወርቅ ቀስ ብላ አይኖቿን ገለጠች። እናቷን አየች። ፈገግ ለማለት ሞከረች፣ ግን አቅም አልነበራትም።

"ውሃ..." አለች።

አዳሙ እየሮጠ ውሃ በጣሳ አመጣ። ቀና አድርጎ ሊያጠጣት ሲሞክር፣ ውሃው ከአፏ ፈሰሰ። የኔወርቅ አንገት ወደ ግራ ዘንበል አለ። የልቧ ትርታ ቆመ።በዚያች ቅጽበት የተሰማው ጩኸት የሻሻትን መንደር አናወጠው። አታለል ፀጉሯን እየነጨች መጮህ ጀመረች። የኔወርቅ ሞት፣ በአዳሙ ቤት እንደ መብረቅ የወረደ ድንገተኛ አደጋ ነበር። አታለል ሬሳውን አቅፋ የምታወጣው ድምፅ የሰው አይመስልም ነበር።

"አትውሰድብኝ!

ገና እኮ ህፃን ናት!

ገና እኮ አላደገችም!“ እያለች ስትታገል፣ የሰፈሩ ሰዎች በግድ ገነጣጥለው አስኬሩን ለሰማይና ለምድር አዘጋጁት።

ሌሊቱ በዋይታ ነጋ። ጎረቤቶች ተሰብስበው፣ የለቅሶ ድንኳን ተተክሎ፣ አዳሙ ወገቡን በሻሽ አስሮ እንባውን እየጠራረገ እንግዳ ይቀበላል። ውስጡ ግን ባዶ ሆኗል። የበኩር ልጁን፣ ያቺን ውሃ አቀባዩን ማጣቱ እንደ ህልም ታይቶታል።

ቀብሩ በቅስት ሀና ቤተክርስቲያን ተፈጸመ። ቀዩ አፈር በኔወርቅ ሳጥን ላይ ሲመለስ፣ አታለል ራሷን ስታ ወደቀች። ውሃ ተርጭቶባት ስትነቃ፣ አለም የዞረችባት መሰላት። ግን፣ እጣ ፈንታ ለዚህች እናት ያዘጋጀችው የመከራ ጽዋ ገና ተቀድቶ አላለቀም ነበር። ከቀብር መልስ፣ ሰዎች አፈር የነካ እጃቸውን በውሃ ታጥበው ወደ ድንኳኑ ሲገቡ፣ አዳሙ ወደ ቤት ውስጥ የገባው ለቀብር ያልሄዱትን ሁለቱን ትናንሽ ልጆቹን ለማየት ነበር። ቤት ውስጥ የጠበቀው ነገር ግን ጉልበቱን አብረከረከው።

መኳንንት እና ይበልጣል፣ ሁለቱም በጠፈሩ አልጋ ላይ በአንድ ላይ እየተንቀጠቀጡ እና ጥርሳቸውን እያፋጩ ተኝተዋል።

"አባዬ... ብርዶኛል...” አለ መኳንንት እየተንተባተበ።
“እማዬን ጥራልኝ...” አለ ይበልጣል በደካማ ድምፅ።አዳሙ ጮኸ። የወንድ ጩኸት። አንጀት የሚበላ፣ ጣራ የሚሰነጥቅ ጩኸት።

"አምላክ ሆይ! ምን አደረግሁህ?

በቃኝ በለኝ እንጂ! አንዷን ቀብሬ ስመለስ፣ ሁለቱን ልትቀበለኝ ደግሰህ ጠበቅከኝ?" ብሎ ደረቱን መታ።

አታለል ከውጭ እየሮጠች ገባች። ልጆቿን ስታይ፣ እብደት የሚመስል ሳቅ ሳቀች። አእምሮዋ መከራውን መሸከም አቅቶት
ነበር።

ደከማቸው አይደል?

ልበሱ... ልበሱ...” እያለች የለበረችውን በጥቁር ቀለም የቀለመ የሀዘን ጨርቅ ነጠላ አውልቃ ደረበችላቸው። ከዚያም ወደ ምድጃው ሄዳ ምድጃውን መምታት ጀመረች። የሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በአዳሙ ቤት ውስጥ የተፈጠረው ነገር በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል። የወባ በሽታ እንደ ርህራሄ ቢስ ወታደር የሁለቱን ህጻናት አካል ወረረው። በዚህ ጊዜ መንደሩ በሙሉ ተረበሸ። "የአዳሙ ቤት ተረገመ" የሚሉ አሉባልታዎች ተወሩ። አንዳንዶች “የአጋንንት ስራ ነው" አሉ፤ ሌሎች “ወባው መላ መንደሩን ሊያጠፋ ነው" ብለው ሰጉ።

አዳሙ እና አታለል እንቅልፍ የሚባል ነገር አጡ። በአንድ በኩል የኔወርቅ ትኩስ መቃብር፣ በሌላ በኩል የሁለቱ ልጆች እጣ ፈንታ።መኳንንት ጠንካራ ልጅ ነበር፤ ከበሽታው ጋር ታገለ። ይበልጣል ግን ገና አምስት አመቱ ስለነበር፣ በሁለተኛው ቀን አቅሙ ተሟጠጠ። ሐሙስ ዕለት፣ ልክ የኔወርቅ ቀብር በሦስተኛው ቀን፣ ይበልጣል እናቱን አፍጥጦ እያየ፣
"እማዬ... የኔወርቅ መጣች... ልንሄድ ነው..." አለ።
ይህ የአታለልን ልብ በሰይፍ እንደመቅደድ ነበር። ከሰዓታት በኋላ የይበልጣል ትንፋሽ ቆመ።
ገና የይበልጣል ሬሳ ሳይወጣ፣ መኳንንት ትንፋሹ ሲያጥር ታየ። አዳሙ፣ አንዱን ልጁን በግራ እጁ፣ ሌላውን በቀኝ እጁ ይዞ በመሃል ቀረ። መኳንንት ወንድሙ ሲሞት አይቷል። ፍርሃት ዓይኑ ላይ ይነበብ ነበር።
"አባዬ አልሙት... አድነኝ..." የሚለው የመጨረሻ ልመናው፣ አዳሙን እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ሲረብሸው የሚኖር ድምፅ ሆነ
በዚያው ምሽት፣ ፀሐይ ሳትወጣ፣ መኳንንትም ተከተለ።
በአንድ ሳምንት ውስጥ... ሦስት አስከሬን።
በአንድ ሳምንት ውስጥ... የሶስት ልጆች ሳቅ ጠፋ።
በአንድ ሳምንት ውስጥ... የአዳሙ እና የአታለል ቤት ወደ መቃብር ቤትነት ተቀየረ።

Seller Information

Please login to view seller contact details.

Please login to view seller contact details.
Share
Please login to express interest in this book.